መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ዓመት ውስጥ ግንቦት 212 ሳሙኤል 13:1-391. ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ለዳዊት ልጅ ለአቤሴሎም አንዲት የተዋበች እኅት ነበረችው፥ ስምዋም ትዕማር ነበረ፤ የዳዊትም ልጅ አምኖን ወደዳት።2. አምኖንም ከእኅቱ ከትዕማር የተነሣ እጅግ ስለ ተከዘ ታመመ፤ ድንግልም ነበረችና አንዳች ያደርጋት ዘንድ በዓይኑ ፊት ጭንቅ ሆኖበት ነበር።3. ለአምኖንም የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ የሚባል ወዳጅ ነበረው፤ ኢዮናዳብም እጅግ ብልህ ሰው ነበረ።4. እርሱም። የንጉሥ ልጅ ሆይ፥ ስለ ምን ቀን በቀን እንዲህ ከሳህ? አትነግረኝምን? አለው። አምኖንም። የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን እወድዳታለሁ አለው።5. ኢዮናዳብም። ታምሜአለሁ ብለህ በአልጋህ ላይ ተኛ፤ አባትህም ሊያይህ በመጣ ጊዜ። እኅቴ ትዕማር እንድትመጣና እኔ የምበላውን እንጀራ እንድትሰጠኝ፥ መብሉንም እኔ እያየሁ እንድታዘጋጅልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላው እለምንሃለሁ በል አለው።6. እንዲሁም አምኖን። ታምሜአለሁ ብሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊያየው በመጣ ጊዜ አምኖን ንጉሡን። እኅቴ ትዕማር እንድትመጣና እኔ እያየሁ ሁለት እንጎቻ እንድታደርግልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላ እለምንሃለሁ አለው።7. ዳዊትም። መብልን ታዘጋጂለት ዘንድ ወደ ወንድምሽ ወደ አምኖን ቤት ሂጂ ብሎ መልእክተኞችን ወደ ትዕማር ቤት ላከ።8. ትዕማርም ወደ ወንድምዋ ወደ አምኖን ቤት ሄደች፥ ተኝቶም ነበር፤ ዱቄትም ወስዳ ለወሰች፥ እያየም እንጎቻ አደረገች፥ ጋገረችም።9. ምጣዱንም ወስዳ በፊቱ ገለበጠች እርሱ ግን ይበላ ዘንድ እንቢ አለ። አምኖንም። ሰውን ሁሉ ከእኔ ዘንድ አስወጡ አለ፤ ሰውም ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ወጣ።10. አምኖንም ትዕማርን። ከእጅሽ እበላ ዘንድ መብሉን ወደ እልፍኙ አግቢው አላት፤ ትዕማርም የሠራችውን እንጎቻ ወስዳ ወንድምዋ አምኖን ወዳለበት እልፍኝ አገባችው።11. መብሉንም ባቀረበች ጊዜ ያዛትና። እኅቴ ሆይ፥ ነዪ ከእኔም ጋር ተኚ አላት።12. እርስዋ መልሳ። ወንድሜ ሆይ፥ አይሆንም፤ እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ዘንድ አይገባምና አታሳፍረኝ፤ ይህንም ነውረኛ ሥራ አታድርግ።13. እኔም ነውሬን ወዴት ልሸከም? አንተም በእስራኤል ዘንድ ከምናምንቴዎች እንደ አንዱ ትሆናለህ፤ እንግዲህስ ለንጉሡ ንገረው፥ እኔንም አይነሣህም አለችው።14. ቃልዋን ግን አልሰማም፤ ከእርስዋም ይልቅ ብርቱ ነበረና በግድ አስነወራት፥ ከእርስዋም ጋር ተኛ።15. ከዚያም በኋላ አምኖን ፈጽሞ ጠላት፤ አስቀድሞም ከወደዳት ውድ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥል በለጠ። አምኖንም። ተነሥተሽ ሂጂ አላት።16. እርስዋም። አይሆንም፤ ቀድሞ ከሠራኸው ክፋት ይልቅ አኔን በማውጣትህ የበለጠ ክፋት ትሠራለህ አለችው፤ እርሱ ግን አልሰማትም።17. የሚያገለግለውንም ብላቴና ጠርቶ። ይህችን ሴት ከፊቴ አስወጥተህ በሩን ዝጋባት አለው።18. ብዙ ኅብር ያለውንም ልብስ ለብሳ ነበር፥ እንዲህ ያለውን ልብስ የንጉሡ ልጆች ደናግሉ ይለብሱ ነበርና፤ አገልጋዩም አስወጥቶ በሩን ዘጋባት።19. ትዕማርም በራስዋ ላይ አመድ ነስንሳ፥ ብዙ ኅብርም ያለውን ልብስዋን ተርትራ፥ እጅዋንም በራስዋ ላይ ጭና እየጮኸች ሄደች።20. ወንድምዋም አቤሴሎም። ወንድምሽ አምኖን ከአንቺ ጋር ነበረን? እኅቴ ሆይ፥ አሁን ግን ዝም በዪ፤ ወንድምሽ ነው፤ ይህን ነገር በልብሽ አትያዢው አላት። ትዕማርም በወንድምዋ በአቤሴሎም ቤት ብቻዋን ተቀመጠች።21. ንጉሡም ዳዊት ይህን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ ነገር ግን የበኵር ልጁ ነበረና ስለ ወደደው የልጁን የአምኖን ነፍስ አላሳዘነም።22. አቤሴሎምም እኅቱን ትዕማርን ስላሳፈራት አምኖንን ጠልቶታልና አቤሴሎም አምኖንን ክፉም ሆነ መልካምም አልተናገረውም።23. ከሁለት ዓመትም በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም አቅራቢያ ባለችው በቤላሶር በጎቹን አሸለተ፤ አቤሴሎምም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ጠራ።24. አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ መጥቶ። እነሆ፥ ባሪያህ በጎቹን ያሸልታል፤ ንጉሡና ሎሌዎቹ ከባሪያህ ጋር ይሂዱ አለው።25. ንጉሡም አቤሴሎምን። ልጄ ሆይ፥ እንከብድብሃለንና ሁላችን እንመጣ ዘንድ አይሆንም አለው። የግድም አለው፥ እርሱ ግን መረቀው እንጂ ለመሄድ እንቢ አለ።26. አቤሴሎምም። አንተ እንቢ ካልህ ወንድሜ አምኖን ከእኛ ጋር እንዲሄድ እለምንሃለሁ አለ። ንጉሡም። ከአንተ ጋር ለምን ይሄዳል? አለው።27. አቤሴሎምም የግድ አለው፥ አምኖንንና የንጉሡንም ልጆች ሁሉ ከእርሱ ጋር ሰደደ።28. አቤሴሎምም እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ግብዣ አደረገ፤ አቤሴሎምም አገልጋዮቹን። አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ ልቡን ደስ ባለው ጊዜ እዩ። አምኖንን ግደሉ ባልኋችሁም ጊዜ ግደሉት፥ አትፍሩም፤ ያዘዝኋችሁም እኔ ነኝና በርቱ ጽኑም ብሎ አዘዛቸው።29. የአቤሴሎም አገልጋዮች አቤሴሎም እንዳዘዛቸው በአምኖን ላይ አደረጉበት። የንጉሡም ልጆች ሁሉ ተነሥተው በየበቅሎቻቸው ተቀምጠው ሸሹ።30. ገናም በመንገድ ሲሄዱ ለዳዊት። አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ገድሎአል፥ ከእነርሱም አንድ አልቀረም የሚል ወሬ መጣለት።31. ንጉሡም ተነሥቶ ልብሱን ቀደደ፥ በምድር ላይም ወደቀ፤ ባሪያዎቹም ሁሉ ልብሳቸውን ቀድደው በአጠገቡ ቆሙ።32. የዳዊትም ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ። ጌታዬ ጕልማሶቹ የንጉሡ ልጆች ሁሉ እንደ ሞቱ አያስብ፤ እኅቱን ትዕማርን በግድ ካስነወራት ጀምሮ በአቤሴሎም ዘንድ የተቈረጠ ነገር ነበረና የሞተ አምኖን ብቻ ነው።33. አሁንም የሞተ አምኖን ብቻ ነው እንጂ የንጉሥ ልጆች ሁሉ ሞቱ ብሎ ጌታዬ ንጉሡ ይህን ነገር በልቡ አያኑር አለው።34. አቤሴሎምም ኰበለለ። ጕበኛውም ጕልማሳ ዓይኑን ከፍ አደረገ፥ እነሆም፥ ብዙ ሰዎች በኋላው በተራራው አጠገብ በመንገድ ሲመጡ አየ።35. ኢዮናዳብም ንጉሡን። እነሆ፥ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፤ ባሪያህ እንዳለው እንዲሁ ሆኖአል አለው።36. ተናግሮም በጨረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ ወዲያው የንጉሥ ልጆች ገቡ፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ደግሞ ንጉሡና ባሪያዎቹ ሁሉ እጅግ ታላቅ ልቅሶ አለቀሱ።37. አቤሴሎም ግን ኰብልሎ ወደ ጌሹር ንጉሥ ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ተልማይ ሄደ። ዳዊትም ሁልጊዜ ለልጁ ያለቅስ ነበር።38. አቤሴሎም ኰብልሎ ወደ ጌሹር ሄደ፥ በዚያም ሦስት ዓመት ያህል ተቀመጠ።39. ንጉሡም ዳዊት ስለ አምኖን ሞት ተጽናንቶ ወደ አቤሴሎም ይሄድ ዘንድ እጅግ ናፈቀ።2 ሳሙኤል 14:1-331. የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ የንጉሡ ልብ ወደ አቤሴሎም እንዳዘነበለ አወቀ።2. ኢዮአብም ወደ ቴቁሔ ልኮ ከዚያ ብልሃተኛ ሴት አስመጣና። አልቅሺ፥ የኀዘንም ልብስ ልበሺ፥ ዘይትም አትቀቢ፥ ስለ ሞተ ሰውም ብዙ ዘመን እንደምታለቅሺ ሁኚ፤3. ወደ ንጉሡም ገብተሽ እንዲህ ያለውን ቃል ንገሪው አላት፤ ኢዮአብም ቃሉን በእርስዋ አፍ አደረገ።4. እንዲሁም የቴቁሔይቱ ሴት ወደ ንጉሥ ገብታ በግምባርዋ በምድር ላይ ወደቀች፥ እጅ ነሥታም። ንጉሥ ሆይ፥ አድነኝ አለች።5. ንጉሡም። ምን ሆነሻል? አላት። እርስዋም መልሳ አለች። በእውነት እኔ ባሌ የሞተብኝ ባልቴት ሴት ነኝ።6. ለእኔም ለባሪያህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፥ በሜዳም ተጣሉ፤ የሚገላግላቸውም አልነበረም፥ አንዱም ሌላውን መትቶ ገደለው።7. እነሆም፥ ዘመዶች ሁሉ በባሪያህ ላይ ተነሥተው። ስለ ገደለው ስለ ወንድሙ ነፍስ እንገድለው ዘንድ ወንድሙን የገደለውን አውጪ አሉኝ፤ እንዲሁም ደግሞ ወራሹን የቀረውን መብራቴን ያጠፋሉ፥ የባሌን ስምና ዘርም ከምድር ላይ አያስቀሩም።8. ንጉሡም ሴቲቱን። ወደ ቤትሽ ሂጂ፥ እኔም ስለ አንቺ አዝዛለሁ አላት።9. የቴቁሔይቱም ሴት ንጉሡን። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ኃጢአቱ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ንጹሕ ይሁን አለችው።10. ንጉሡም። የሚናገርሽን አምጪልኝ፥ ከዚያም በኋላ ደግሞ አይነካሽም አለ።11. እርስዋም። ደም ተበቃዮችም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳያጠፉ ልጄንም እንዳይገድሉ፥ ንጉሡ አምላኩን እግዚአብሔርን ያስብ አለች። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! ከልጅሽ አንድ ጠጕር በምድር ላይ አይወድቅም አለ።12. ሴቲቱም። እኔ ባሪያህ ለጌታዬ ለንጉሥ አንድ ቃል ልናገር አለች፤ እርሱም። ተናገሪ አለ።13. ሴቲቱም አለች። በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ስለ ምን አሰብህ? ንጉሡ ይህን ነገር ተናግሮአልና ያሳደደውን ስላላስመለሰ በደለኛ ነው።14. ሁላችን እንሞታለን፥ በምድርም ላይ እንደ ፈሰሰና እንደማይመለስ ውኃ ነን፤ እግዚአብሔርም የነፍስን ጥፋት አይወድድም፥ ነገር ግን የተጣለ ሰው ፈጽሞ እንዳይጠፋ በምክሩ ያስባል።15. አሁንም ሕዝቡ ስለሚያስፈራኝ ይህን ነገር ለጌታዬ ለንጉሥ እነግረው ዘንድ መጥቻለሁ፤ እኔም ባሪያህ። ምናልባት የእኔን የባሪያውን ልመና ንጉሡ ያደርግልኝ እንደሆነ ለንጉሡ ልናገር፤16. እርስዋንና ልጅዋን ከእግዚአብሔር ርስት ያጠፋቸው ዘንድ ከሚሻ ሰው እጅ ያድን ዘንድ ንጉሡ ባሪያውን ይሰማል አልሁ።17. እኔም ባሪያህ። መልካሙንና ክፉውን ነገር ለመስማት ንጉሡ ጌታዬ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነውና የጌታዬ የንጉሡ ቃል ያጽናናኛል፤ አምላክህም እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን አልሁ።18. ንጉሡም ለሴቲቱ መልሶ። የምጠይቅሽን ነገር አትሰውሪኝ አላት። ሴቲቱም። ጌታዬ ንጉሥ ይናገር አለች።19. ንጉሡም። በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ ከአንቺ ጋር ነውን? አላት። ሴቲቱም መልሳ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ጌታዬ ንጉሥ ከተናገረው ነገር ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሊል የሚችል የለም፤ ባሪያህ ኢዮአብ አዝዞኛል፥ ይህንም ቃል ሁሉ በባሪያህ አፍ አደረገው።20. ባሪያህ ኢዮአብ የዚህ ነገር መልክ እንዲለወጥ አደረገ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ጠቢብ እንደ ሆነ፥ አንተም ጌታዬ በምድር ላይ ያለውን ነገር ሁሉ ታውቅ ዘንድ ጠቢብ ነህ አለች።21. ንጉሡም ኢዮአብን። እነሆ፥ ይህን ነገር አድርጌአለሁ፤ እንግዲህ ሂድና ብላቴናውን አቤሴሎምን መልሰው አለው።22. ኢዮአብም በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ እጅ ነሣ፥ ንጉሡንም ባረከ፤ ኢዮአብም። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የባሪያህን ነገር አድርገሃልና በዓይንህ ፊት ሞገስ እንዳገኘ ባሪያህ ዛሬ አወቀ አለ።23. ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ ጌሹር ሄደ፥ አቤሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም ይዞ መጣ።24. ንጉሡም። ወደ ቤቱ ይሂድ እንጂ ፊቴን እንዳያይ አለ፤ አቤሴሎምም ወደ ቤቱ ሄደ፥ የንጉሡንም ፊት አላየም።25. በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ እንደ አቤሴሎም በውበቱ የተመሰገነ ሰው አልነበረም፤ ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር አልነበረበትም።26. ጠጕሩም ይከብደው ነበርና በዓመት አንድ ጊዜ ይቈርጠው ነበር፤ ሲቈረጥም የራሱ ጠጕር በንጉሥ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ያህል ይመዘን ነበር።27. ለአቤሴሎምም ሦስት ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት፤ የሴቲቱም ልጅ ስም ትዕማር ነበረ፥ እርስዋም የተዋበች ሴት ነበረች።28. አቤሴሎምም በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ሙሉ የንጉሡን ፊት ሳያይ ተቀመጠ።29. አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ ይልከው ዘንድ ወደ ኢዮአብ ላከ፥ ወደ እርሱም ሊመጣ አልወደደም፤ ሁለተኛም ላከበት፥ ሊመጣ ግን አልወደደም።30. ባሪያዎቹንም። በእርሻዬ አጠገብ ያለውን የኢዮአብን እርሻ እዩ፥ በዚያም ገብስ አለው፤ ሂዳችሁ በእሳት አቃጥሉት አላቸው። የአቤሴሎምም ባሪያዎች እርሻውን አቃጠሉት።31. ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ አቤሴሎም ወደ ቤቱ መጣና። ባሪያዎችህ እርሻዬን ስለምን አቃጠሉት? አለው።32. አቤሴሎምም ኢዮአብን መልሶ። ከጌሹር ለምን መጣሁ? በዚያም ተቀምጩ ብሆን ይሻለኝ ነበር ብለህ እንድትነግረው ወደ ንጉሡ እልክህ ዘንድ ወደ እኔ ጠራሁህ፤ አሁንም የንጉሡን ፊት ልይ፥ ኃጢአት ቢሆንብኝ ይግደለኝ አለው።33. ኢዮአብም ወደ ንጉሥ መጥቶ ነገረው፤ አቤሴሎምንም ጠራው፥ ወደ ንጉሡም ገብቶ በንጉሥ ፊት ወደ ምድር በግምባሩ ተደፋ፤ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው።መዝሙር 66:1-71. በምድር ያላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፥2. ለስሙም ዘምሩ፥ ለምስጋናውም ክብርን ስጡ።3. እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት። ሥራህ ግሩም ነው፤ ኃይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶች ዋሹብህ።4. በምድር ያሉ ሁሉ ለአንተ ይሰግዳሉ፥ ለአንተም ይዘምራሉ፥ ለስምህም ይዘምራሉ።5. ኑ የእግዚአብሔርንም ሥራ እዩ፤ ከሰው ልጆች ይልቅ በምክር ግሩም ነው።6. ባሕርን የብስ አደረጋት፥ ወንዙንም በእግር ተሻገሩ፤ በዚያ በእርሱ ደስ ይለናል።7. በኃይሉ ለዘላለም ይገዛል፤ ዓይኖቹ ወደ አሕዛብ ይመለከታሉ፤ ዓመፀኞች ራሳቸውን ከፍ ከፍ አያድርጉ።ምሳሌ 16:25-2625. ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።26. የሠራተኛ ራብ ለእርሱ ይሠራል፥ አፉ ይጐተጕተዋልና።ዮሐንስ 6:52-7152. እንግዲህ አይሁድ። ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ።53. ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።54. ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።55. ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና።56. ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።57. ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል።58. ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በልተው እንደ ሞቱ አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል59. በቅፍርናሆም ሲያስተምር ይህን በምኵራብ አለ።60. ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎች በሰሙ ጊዜ። ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል? አሉ።61. ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንዳንጐራጐሩ በልቡ አውቆ አላቸው። ይህ ያሰናክላችኋልን?62. እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?63. ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።64. ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ። ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ ከመጀመሪያ ያውቅ ነበርና።65. ደግሞ። ስለዚህ አልኋችሁ፥ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም አለ።66. ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም።67. ኢየሱስም ለአሥራ ሁለቱ። እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን? አለ።68. ስምዖን ጴጥሮስ። ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤69. እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት።70. ኢየሱስም። እኔ እናንተን አሥራ ሁለታችሁን የመረጥኋችሁ አይደለምን? ከእናንተም አንዱ ዲያብሎስ ነው ብሎ መለሰላቸው።71. ስለ ስምዖንም ልጅ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ ተናገረ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነ እርሱ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ አለውና። Amharic Bible (Selassie) 1962 Selassie 1962: © United Bible Societies 1962